በኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በደብረ ብርሃን ከተማ ምእመናን የተገነባው የጠባሴ
ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ዘመናዊ ካቴዲራል ቤተ ክርስቲያን ግንባታው ተጠናቆ በብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት ባርኮት
ታቦተ ህጉ ከመቃኞ ወደ አዲሱ ቤተ መቅደስ ገብቶ ሥርዓተ ንግሱ በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ውሏል።
በበዓሉ ላይ ለተገኙት ምእመናን በብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ፣ በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ እና በብፁዕ አቡነ ኤፍሬም ጸሎተ ቡራኬና ቃለ ምዕዳን ተሰጥቷል።
ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያና የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት አባታዊ ቡራኬ "እስመ አንትሙሰ ለግዕዛን ተጸዋእክሙ" የሰው ልጅ አዕምሮው መልካም ሲሆን ለእግዚአብሔር ምቹ ሆኖ ይገኛል፣ የሰው ልጅ አዕምሮ ኃያል ረቂቅና ምጡቅ አፈጣጠሩም ክቡር ነው ያሉት ብፁዕነታቸው የሰው ልጅ አዕምሮ መልካም ሲያስብ አምላካችን እግዚአብሔርም ለሀገራችን ፣ ለምድራችንና ለዓለማችን ሰላሙን ፍቅሩንና አንድነቱን ያድለናል ብለዋል።
የክርስቲያኖች አዕምሮ የለሰለሰ መሬት ሲሆን ይኽም ሰላሳ ስልሳና መቶ ፍሬ ያፈራል በዚህ ቅዱስ ስፍራ የተሰበሰባችሁ የእግዚአብሔር
ልጆች የፍቅርና የበረከት መገኛ ታላላቆቹ አባቶቻችን በመስዋዕትነት ያቆይዋት ታላቅ ሀገር መልካም ፍሬ የምታፈሩ የለሰለሰ መሬት ናችሁ ደግነትንና ርህራሄን የተላበሳችሁ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ናችሁ ይኽን በጎነታችሁን በማጽናት እስከ መጨረሻው ጽኑአን ሁኑ ሲሉ መክረዋል።
ብፁዕነታቸው ይኽንን ዘመናዊ ቤተ ክርስቲያን በገንዘብ ፣ በዕውቀት ፣ በሀሳብና በአይነት አስተዋጽኦ ላባረከቱ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል።
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የስብከተ ወንጌል ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የመገናኛ ብዙኀን ስርጭት ድርጅት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ቃለ ቡራኬ ደጆችሽ አይዘጉም ፣ እርሱ እግዚአብሔር ብርሃንሽ ነውና ፣ ፀሐይሽ አይጨልምም ፣ ከዋክብት ካህናትሽ በውስጥሽ ያመሰግኑሻል ፣ ነፋሳት ቢነፍሱ ዝናባት ቢዘንቡ ጎርፍም ቢጎርፍ አያናውጥሽም መሠረትሽ በዓለት የተመሰረተ ነው ያሉት ብፁዕነታቸው ጊዜያዊ ቤታችንን የቱንም ያህል አሳምረን ብንሰራ ልጆች ሊካሰሱበት ይችላሉ ዘላለማዊ ማረፊያችሁን እንዲህ አሳምራችሁ በመስራታችሁ ክብር ይገባችኋል ብለዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም እናንተ የነዘርዐ ያዕቆብ ፣ የነእምዬ ምኒልክ ልጆች ስለሆናችሁ የአባቶቻችሁን መልካምነት የወረሳችሁ የሰላም መምህራን ናችሁም ብለዋል ምእመናኑን።
ብፁዕነታቸው ወጣቱ ትውልድ አባቶቻችሁ በሬ አርደው ፣ እንግዳ ተቀብለው ፣ ጎረቤት ጠርተው ዝክር በሚያዘክሩበት ቢለዋ እርስ በርሳችሁ አትተራረዱ ፣ ወላጆቻችሁ ተምሮ ተመርቆ ይመጣል ብለው በጉጉት ሲጠብቁ አስከሬናችሁን አይቀበሉ፣ በድንጋይም አትጋደሉ ዲንጋዩን ቤተ መቅደስ አንጹበት ሲሉ መክረዋል።
የዕለቱን ወንጌል ያስተማሩት የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ስራ አሥኪያጂ መጋቤ ሐዲስ ነቅዐጥበብ አባቡ "ወአጥፍዑ ኃይለ እሳት፣የእሳትን ኃይል አጠፉ" በሚል ርዕስ በሰጡት ትምህርት እለእስክንድሮስ የተባለ ንጉስ ቅድስት ኢየሉጣንና ህጻኑ ቅዱስ ቂርቆስን እምነታችሁን ካልቀየራችሁ እገድላችኋለሁ ብሎ እንዳስገደዳቸው አውስተው በእምነታቸው በመጽናታቸው ንጉሱ በፈላ ውሃ ሊገድላቸው ትእዛዝ ሰጥቷል ብለዋል።
እኔስ ልሙት ይኽን ህጻን ልጅ ምን ላድርገው ብላ ስትጨነቅ አይዞሽ እናቴ ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ያወጣ እኛንም ያድነናል ብሎ እናቱን እንዳበረታታት ገልጸው ንጉሱ ወደ አሰፍላው ውሃ ቢወረውሯቸው እመቤታችንን ለማብሰር ዳንኤልን ከአፈ አናብስትና ሠለስቱ ደቂቅን ከእቶነ እሳት ያዳናቸው ፈጥኖ ደራሹ ቅዱስ ገብርኤል ከፈላው ውሃ በማዳን ከሞት መዳፍ ነጥቆ በቅድስናው ሰገነት በሞት መካከል ህይወት እንዳለ ያዬንበት የድኅነት ቀን መሆኑን በስፋት አስተምረዋል።