Thursday, December 24, 2020

በቀወት ወረዳ እና በሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ለሁለት ቀናት በተለያዩ ዘርፎች ሥልጠና ተሰጠ።

 በቀወት ወረዳ እና በሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ለሁለት ቀናት በተለያዩ ዘርፎች ሥልጠና ተሰጠ።

ሥልጠናው ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያና የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት የሥራ መመሪያ ተሰጥቷል።

ብፁዕነታቸው ስለሚሥጥራተ ቤተ ክርስቲያን አፈጻጸም እና ትርጓሜ ጥልቅ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ሚሥጢር ማለት ድብቅ ፣ ሽሽግና ለሁሉም የማይገለጥ እንደሆነና በስጋዊ አመለካከት የማይታዩ ሀብትና በረከት የሚያስገኙ የመንፈስ ቅዱስ ሀብት ናቸው ብለዋል።

አንዳንድ ካህናት ኃላፊነትን ሳይረዱ ለክህነት መብቃት ፣ ክህነትን እንደተቀበሉ ቀኖና አለመፈጸም እና የክህነት መስፈርትን ሳያሟሉ ካህን ሆኖ መገኘት ዋና ዋና የቤተ ክርስቲያን ፈተና መሆናቸውን ገልጸው ካህናት ልጆቻቸውን መንፈሳውይ ትምህር ማስተማር እንዳለባቸውና ሚሥጢራትን በአግባቡ መፈጸም እንደሚገባቸው አስተምረዋል።

ካህን ለሁሉም ምእመናን እኩል የሚጨነቅ አዛኝ ርህሩህና ሻማ ሆኖ ለሌላው ብርሃን መሆን አለበት ያሉት ብፁዕነታቸው ጌታችን ሐዋርያትን እናንተ የምድር ጨው ናችሁ እንዳላቸው እናንተም ካህን በአደባባይ ሲናገር በመንፈሳዊ እና በሳይንሳዊ እውቀት የበለጸገ እውቅት ይዞ እንደጨው አልጫውን ዓለም የሚያጣፍጥ መሆን አለበት ብለዋል።

ብፁዕነታቸው ትምህርተ ኖሎትን አስመልክተው በሰጡት ትምህርት ከሰማይ እስከ ምድር ፣ ከባህር እስከ የብስ ፣ ከሚታየው እስከ እማይታየው ከግዙፉ እስከ ረቂቅ ያሉ አጠቃላይ ፍጡራን አምላካዊ እና መልአካዊ ጥበቃ እንዳላቸውና እግዚአብሔር በሚመርጣቸው ሰዎች ደግሞ ለሰው ልጆች ሰብዓዊ ጥበቃ አለው ብለዋል።

ካህናት የተሰጣቸውን ልጆቻቸውን የመጠበቅ ሐዋርያዊ ኃላፊነትና መለኮታዊ ሥልጣን በአግባቡ በመወጣት በየትኛውም ሀይማኖታዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች ሁሉ በመገኘት እና አርአያ ክህነትን በመጠበቅ ከትዕቢት ፣ ከፍቅረ ንዋይ እና ከቸልተኝነት በመራቅ ለምእመናን ሐዋርያዊ አገልግሎት በትጋት መስጠት እንዳለባቸው አስተምረዋል።

በተያያዘም በመምህር ሲገኝ ሀብተ ወልድ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ቁጥጥር መምሪያ ኃላፊ ስለሂሳብ ሰነድ አያያዝና አሰራር ፣ ስለቢሮ አደረጃጀት ፣ ስለገቢና ወጪ ሂሳብ አያያዝና አጠቃቀም በመለከተ እና ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን ገቢ በህጋዊ ደረሰኝ ገቢና ወጭ መደረግ እንዳለበት እና በመምህር ሰይፈ በየነ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ ስለክብረ ክህነት በስፋትና በጥልቀት ሥልጠና ተሰጥቷል።


ፈጣን መረጃ ለማግኘት የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ