Sunday, December 27, 2020


 

በየዓመቱ ታኅሣሥ 19 ቀን በመላው ኦርቶዶክሳዊያን በታላቅ ድምቀት የሚከበረውን የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤልን በዓል

 በየዓመቱ ታኅሣሥ 19 ቀን በመላው ኦርቶዶክሳዊያን በታላቅ ድምቀት የሚከበረውን የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤልን በዓል አስመልክተው የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስጊያጅ ክቡር መጋቤ ሐዲስ ነቅዐ ጥበብ አባቡ " ቅዱስ ገብርኤል እነሆ እየበረረ መጣ" ትን.ዳን 9:21 በሚል ርእስ ትምህርተ ወንጌል አስተላልፈዋል።

እኛም የክቡር ሥራ አስጊያጁን ሙሉውን ትምህርተ ወንጌል እነሆ ብለናል ፤ መልካም በዓል እንዲሆንላችሁም ተመኝተናል።

የተወደዳችሁ በሀገር ውስጥ የምትኖሩ ኢትዮዽያውያን እና ከሀገር ውጪ የምትኖሩ ትውልደ ኢትዮዽያውያን የመልአኩ ወዳጆች ኦርቶዶክሳውያን እና ኦርቶዶክሳውያት በሙሉ እንኳን ለታላቁ መልአክ ለቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ።

የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በድምቀት ከምታከብራቸው ክብረ በዓላት አንዱ የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እንደ መሆኑ መጠን በዓሉ በቤተ ክርስቲያናችን ሕግ እና ሥርዓት መሠረት በስፋት እና በድምቀት የሚከበር ሲሆንበበዓሉ ላይም የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል አማላጅነት ተራዳኢነት በስፋት ይወሳል።

ቅዱስ ገብርኤል እነሆ እየበረረ መጣ ትን ዳን 9:21 ይህንን ኀይለ ቃል ነቢዩ ዳንኤል በጊዜው የነበረ መሪ ሕዝቡን ሲያስጨንቅ አይቶ በመራድ በመንቀጥቀጥ በእግዚአብሔር ፊት ሱባኤ ገብቶ ስለ ሕዝቡ እያለቀሰ እያነባ ሲማጸን አስቀድሞ በራእይ የሚያውቀው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ እየበረረ መጥቶ ከወደቀበት እንዳነሳው እና የፈሰሰው እንባውን እንዳበሰለት በደስታ የተደረገለትን በመመስከር ያስተምረናል ።

ዛሬ በምናከብረው በዓል ላይ መልአኩ ስላደረገው ድንቅ ተአምር ትንሽ እንመልከት የፋርስ ባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር ወደ ኢየሩሳሌም ዘምቶ ንዋያተ ቅድሳቱን ዘርፎ ሕዝቧን ማርኮ ወደ ሀገሩ እንደተመለሰ ትን ዳን 1 :1 ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል ። ከምርኮኞቹም መካከል ነቢዩ ዳንኤል እና ሠለስቱ ደቂቅ ይገኙበታል ።

እነዚህ የተማረኩ ነቢዩ ዳንኤል እና ሠለስቱ ደቂቅም በተማረኩበት ሀገር አራት ታላላቅ ፈተናዎች ወደ ሕይወታቸው መጥተውባቹው ሦስቱን በጥበብ በማስተዋል ማለፍ ሲችሉ አንዱን ግን በምንም በምን የማያልፉት ሆኖ ስላገኙት ነፍሳቸውን ለእግዚአብሔር አደራ ሰጥተው ተፋልመውታል

አንደኛው ፈተና ስማችሁ ይቀየር ነበር ዳንኤል አናንያ ሚሳኤል አዛርያ ተብለው በስመ እግዚአብሔር ትርጓሜ ይጠሩ የነበሩ አይ የለም ለጣኦቶቻችን በሚመች ስም መጠራት አለባችሁ ሲባሉ ወጣቶቹም ይሁን የማይቀየረው የእግዚአብሔር ስም አይቀየር እንጂ የእኛ ችግር የለውም ብለው ብልጣሶር ሲድራቅ ሚሳቅ አብደናጎ ተብሎ ስማቸው ተቀይሮ የመጀመሪያውን ፈተና አልፈዋል ።

ሁለተኛው ፈተና ከተማረኩት ሰዎች መካከል ከነገሥታት ከመሳፍንት ወገን ዘር ያላቸው መልከ መልካም የሆኑ ለጥበብ የሚመቹ የሀገሩን ቛንቋ ባህል እንዲማሩ እነዚሁ ወጣቶች የተሻሉ ሆነው በመገኘታቸው የትምህርት እድል አግኝተው ንጉሡ ከሚጠጣው እየጠጡ ከሚበላው እየበሉ እንዲማሩ ዕድል ቢያገኙም እነሱ ግን የለም ባህላችን ከባህላቸው ስለማይገናኝ ቆሎ እየቆረጠምን ውሀ እየተጎነጨ እንማር ብለው አሳላፊያቸውን ቢጠይቁት ንጉሡን ፈርቶ እንቢ ቢላቸውም ለአሥር ቀን ፈትነን በማለት በአሥር ቀናቸው ሲታዩ ጮማ ከሚቆረጥላቸው ጠጅ ከሚንቆረቆርላቸው ሰዎች ይልቅ የነሱ ፊት አምሮ ሰውነታቸው ወፍሮ ተገኝቷል በዚህም የቆሎ ትምህርት ቤት ሕይወትን አስጀምረው ሁለተኛውን ፈተና አልፈዋል ።

ሦስተኛው ፈተና ንጉሡ ህልም አየሁ ህልሙም ትርጓሜውም ጠፋኝ ስለዚህ ህልሜን ከነትርጓሜው አምጡ ካላመጣችሁ ሞት ይገባችኋል ብሎ በአስማተኞቹ ላይ የሞት አዋጅ ባወጀበት ሰአት ለነዚህ ወጣቶች የጥበብ ባለቤት እግዚአብሔር ህልሙን ከነትርጓሜው ገልጦላቸው ለንጉሡ አቅርበው እነሱን እና ጠቢባኑን ከሞት ታድገው ፈተናውን አልፈዋል ።


አራተኛው እና የማይታለፈው ፈተና ንጉሡ ናቡከደነጾር በዱራ ሜዳ ላይ የወርቅ ምስል አቁሞ ለዚህ ላቆምኩት ምስል እንድትሰግዱ መለከት እንቢልታ ሲነፋ ስገዱ ያልሰገደ ቢኖር ግን ወደ እቶን እሳት ይጣላል ብሎ አዋጅ አወጀ በአዋጁም መሠረት ሁሉም ላቆመው የወርቅ ምስል ሲሰግድ ስግደት ለአምላካችን እንጂ ለዚህ አንሰግድም ብለው እንቢ አሉ።

ውዲያው ለንጉሡ እነዚህ በግዛትህ የሾምካቸው ሰለስቱ ደቂቅ ላቆምከው ምስል አንሰግድም አሉ ብለው ከሰሷቸው ንጉሡም ነገሩ እውነት ነውን ብትሰግዱ ይሻላችኋ ባትሰግዱ ግን ወደ ሚነድ እሳት ትጣላላችሁ ከእጇ የሚያድናችሁ አንዳች የለም ሲላቸው አዎ አንሰግድም ማለታችን እውነት ነው በዚህ ነገር እንመስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም አንተን እና እኛን የፈጠረ ከሚነደው እሳት ያድነናል በሰማእትነት ሞተን መንግሥቱን እንድንወርስ ሽቶ እንኳን ባያድነን አንተ ላቆምከው ጣኦት አንሰግድም ብለውታል።

በዚህ ጊዜ ንጉሡ ተናዶ በሉ ከነ ልብሳቸው ጠቅላችሁ ወደ ሚነደው እቶን ጣሉልኝ ብሎ አዞ ወደ እቶኑ ቢጣሉ የልብሳቸው ዝሀ የጸጉራቸው ዘለላ እንኳን አንዳች አልነካውም ይልቁንም እነሱን ወደ እሳቱ የጣሉትን ሰዎች እሳቱ አቃጥሏቸዋል እነሱ ግን ገና ወደ እሳቱ ሲጣሉ መልአኩ እየበረረ መጥቶ በመስቀሉ ሲባርከው ነበልባሉ እንደ ሀመልማል ቀዝቅዟል በእሳቱም ውስጥ እግዚአብሔርን አመስግነዋል።

ንጉሡም ትናት ሦስት ሰዎች ወደ እቶን ጥለን ነበር እንዴት ሆነው ይሆን አመድ ትቢያ ሆነዋል ብሎ በሰገነቱ ብቅ ብሎ ሲመለከት አራት ሁነው እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ ይህ ነገር ምንድነው ትናት ሦስት ነበሩ ዛሬ ደግሞ አራት ናቸው እንዲያውም አራተኛው የእግዚአብሔርን ልጅ ይመስላል ብሎ ተደንቆ ወደ እቶኑ መጥቶ እንዴት ከእሳቱ ተረፋችሁ ቢላቸው አምላካችን መልአኩን ልኮ አዳነን ሲሉት ኑ ውጡ ካሁን በኋላ በግዛቴ ሁሉ የዳንኤል የአናንያ የሚሳኤል የአዛርያ አምላክ ይመለካል ከርሱ ሌላ ሌላ አምላክ የለም ብሎ አዋጁን በአዋጅ ሽሮ አስተካክሏል።መልአኩ የቅዱስ ገብርኤልም እየበረረ መጥቶ ማዳን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በእውነት ያለ ሀሰት ይነገራል ስለዚህ ዛሬም በዓለማች በሀገራችን እየነደደብን ያለውን የዘረኝነት እሳት የጥላቻ እሳት የመገዳደል የመለያየት እሳት የመገፋፋት የመተማማት እሳት ቅዱስ ገብርኤል እየበረረ ወደ ሕይወታችን መጥቶ ያጥፋልን።

ወደ ነቢዩ ዳንኤል እየበረረ መጥቶ ከወደቀበት አንስቶ እንባውን ያበሰለት ወደ ሠለስቱ ደቂቅ እየበረረ መጥቶ ከሚነደው እሳት ያዳናቸው ወደ እነ ካህኑ ዘካርያስ እየበረረ መጥቶ ጸሎታቸውን የተቀበላቸው ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም እየበረረ መጥቶ የምስራቹን ያበሰራት ወደ እነ ኢየሉጣ እየበረረ መጥቶ ከፈላ ውሀ ያዳናቸው ታላቁ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ሁላችንም ሕይወት በአማላጅነቱ እየበረረ መጥቶ ከከበን መከራ እና ሥቃይ ሁሉ ይታደገን።

የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት የመልአኩ ተራዳኢነት ከሁላችን ጋር ይሁን ።

ቅዱስ ገብርኤል እነሆ እየበረረ መጣ !!!

መልካም በዓል !!!

መጋቤ ሐዲስ ነቅዐ ጥበብ ዘሸዋ ደብረ ብርሃን!!

18/04/13 ዓም !!

ሸዋ ደብረ ብርሃን ኢትዮዽያ !!

ፈጣን መረጃ ለማግኘት የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ

https://t.me/EOTCNSD