የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ ነቅዐጥበብ አባቡ የደብረ ታቦር ዓመታዊ በዓል አስመልክተው የእንኳን ከደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
ሥራ አስኪያጁ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በዓሉ ከዘጠኙ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢሱስ ክርስቶስ ዐበይት በዓላት አንዱ መሆኑን ገልጸው ሐዋርያትን ጌታችን ሰዎች ማን ይሉኛል ብሎ ሲጠይቃቸው ከፊሉ ሙሴ ፣ ከፊሉ ኤልያስ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል ብለውት ስለነበረ ሙሴን ከብሄረ ሙታን ፣ ኤልያስን ከብሄረ ህያዋን አምጥቶ የኤልያስና የሙሴ አምላክ እንጂ ኤልያስም ሙሴም አለመሆኑን የገለጸበት ታላቅ ምስጢር አዘል በዓል መሆኑን ገልጸዋል።
ቅዱስ ጴጥሮስም ይኽን ባዬ ጊዜ ጌታ ሆይ እንደቀድሞው ኤልያስ እሳት እያዘነበ ሰማይ እየለጎመ ፣ ሙሴ ባህር እየከፈለ ጠላት እየገደለ መና እያወረደ አንድ ለሙሴ አንድ ለኤልያስ አንድ ላንተ ቤት ሰርተን ለእኛ በዚህ መኖር መልካም ነው ብሎ እንደጠየቀና ክርስቲያን ራሱን እንደማያስቀድም ትምህርት የተማርንበትም በዓል ነው ብለዋል።
ምእመናን በዓሉን ኅብስት በመጋገርና ለዘመድ አዝማድ በመላክ ፣ ችቦ በማብራትና ጅራፍ በማጮኽ በጋራ እንደሚያከብሩት የገለጹት መጋቤ ሐዲስ ነቅዐጥበብ ታሪካዊ ዳራውን ሲያብራሩ ኅብስቱ (ሙልሙሉ) በደብረ ታቦር ተራ በተገለጠው ብርሃን ወደ ቤታቸው ላልተመለሱ እረኞች የሄደላቸው ስንቅ ሲሆን ችቦው የተገለጠው ብርሃን ምሳሌና ጅራፉ የእግዚአብሔር አብ የጅራፉ ድምፅ የእግዚአብሔር አብ ድምፅ ምሳሌ መሆኑ አብራርተዋል።
በዓሉ ምእመናን በጋራ የሚያከብሩት ማኅበራዊ ዕሴቱ የጎላ በመሆኑ ሀይማኖታዊ ይዘቱን እና ታሪካዊነቱን ጠብቀን ለትውልድ ልናስተላልፈው ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።