ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስና ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በሸዋ ሮቢት ከተማ በቅዱስ ቴዎድሮስ ካቴዲራል ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ለምእመናን ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ ሰጡ።
ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪና የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንትና የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሸዋ ሮቢት ከተማ ቅዱስ ቴዎድርስ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ለምእመናን ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ ሰጥተዋል።
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ በቦታው ሲደርሱ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ፣ በሰንበት ትምህርት ዘማርያንና በርካታ ምእመናን በዝማሬ ፣ በእልልታና በጭብጨባ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ ሁሉን ማድረግ የሚቻለው አምላካችን በፍቅሩ ስቦ በረድኤት ጠብቆ የበረከት ፣ የፍቅርና የሰላም ተምሳሌት ከሆናችሁት የሸዋ ሮቢት ምእመናን ጋር በመገናኘታችን ደስ ብሎናል እናንተም እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
እናንተ ከክፉ ነገር የራቀ የመልካም ነገገር የሁሉ መጠለያና ማረፊያ የተባረከ የመንገድ ዳር ሾላ ናችሁ ፤ በካህናትና በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት በኔ ኑሩ እኔም በእናንተ እኖራለሁ የሚለውን አምላካዊ ቃል በመፈጸም ጣፋጭ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የህይወት ልምላሜ የታዬባችሁ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር የለዩ የቅዱሳን አባቶቻችን ልጆች ናችሁ ብለዋል።
በተመሳሳይ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በሰጡት ቃለ ምዕዳንና ባስተላለፉት መልእክት ዘመናትን አሳልፎ የሚኖር ኃጢአትና በደላችንን ሳይቆጥር በእድሜያችን ላይ ይኽን ጊዜ ጨምሮ ከጨለማ ወደ ብርሃን እንድንሸጋገር ያደረገ በቅድስናው ስፍራ በሰማያዊት ምድር ተሰብስበን ስሙን እንድናመሰግን የፈቀደልን የቅዱሳን አምላክ ክብርና ምስጋና ይግባው ብለዋል።
"ልጆቼ ሆይ ታገለግሉት ዘንድ ከፊቱም ቀርባችሁ ለእርሱ በመታመን መልካሙንና በጎ ነገርን ትፈጽሙ ዘንድ እርሱ እግዚከብሔር መርጧችኋልና ቸል አትበሉ" በሚል ርዕስ የቀድሞዎቹ አባቶቻችን በፍቅርና በመተባበር የነበራቸውን አምልኮተ እግዚአብሔርን አሁን ያሉት አንዳንዶች ይኽንን ትተው የበጎ ሥራ መንገዶች ተቆፋፍረውና የአመጽ መንገዶች ተከፍተው የሰው ልጅ ከአምላኩ ይልቅ ስልጣን፣ ገንዘብንና ሰውን መደገፍ ቢጀምርም ሁሉም የሚያልፉ በመሆናቸው ይወድቃሉ እግዚአብሔርን የሚደገፉ ግን አይወድቁም አያቶቻችሁን ዋኖቹን አስቡ ብለዋል።
ምእመናን በችግር መካከል የበቀልን ነን ችግር ዙሪያችንን ከቦናል መልካምም ነገር አንሰማም ስናለቅስ እንባችንን የሚያብስልን ሳይሆን በልቅሷችን ላይ ሌላ ሀዘን ይጨምሩብናል ነገር ግንጌታችንና አምላካችን አይዛችሁ ልባችሁ አይታወክ በእኔ እመኑ እኔም ከእናንተ ጋር እሆናለሁ አባት እንደሌለው ልጅ አልተዋችሁም ብሏልና እግዚአብሔር ሕዝቡን ነጻ ለማውጣት ሠራዊት አይመለምልም ሲሉ ምእናኑን መክረዋል።
ፈጣን መረጃ ለማግኘት የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ
https://t.me/EOTCNSD
website: https://eotcnorthshoadiocese.blogspot.com/