Sunday, November 22, 2020

በ፰ ነጥብ ፪ ሚሊዮን ብር የሕንጻ እድሳት

በከተማዋ ነዋሪዎችና በአካባቢው ተወላጆች በ፰ ነጥብ ፪ ሚሊዮን ብር የሕንጻ እድሳትና የማስፋፊያ ስራ የተደረገለት የመሐል ሜዳ ደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴዲራል በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተባርኮ ቅዳሴ ቤቱ በዛሬው ዕለት በታላቅ ድምቀት ተከበረ።

የቅዱስ ሚካኤል ጽላት ከ፲ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በደዋት ልደታ በድርብነት የነበረ ሲሆን በ1947 ዓ.ም እንደተመሰረተች የሚነግራላት ባለዘመናዊ ፕላኗ መሀል ሜዳ ከተማ ምእመናን ጥያቄ አሁን ባለበት የከተማ እምብርት የተተከለው ካቴዲራሉ በተለያዩ ጊዜያት ግንባታው ሲካሄድ ቆይቶ ባጋጠመው የግንባታ የጥራት ችግር በ፰ ነጥብ ፪ ሚሊዮን ብር የሕንጻ እድሳትና ማስፋፋት ተደርጎለት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ በርካታ ሊቃውተ ቤተ ክርስቲያን እና በ፲ሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናን በተገኙበት በዛሬው ቤተ መቅደሱ ከዓመታዊ ክብረ በዓሉ ጋር ተቀናጅቶ በታላቅ ድምቀት ተክብሯል።

በክብረ በዓሉ ላይ ለተሰበሰቡት ምእመናን ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፓትያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያና የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የበላይ ጠባቂና የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ አስተላልፈዋል።

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ የደስታ ቃል በጻድቃንና በደጋጎች ቤት ነው ፤ በጎና መልካም የሆነ ለሀገር የሚበጅ ስራ የሚሰሩ ሰዎች በረከተ እእግዚአብሔር በቤታቸው ነው ፣ ቆራጦችና ደጋጎቹ የእግዚአብሔር ሰዎች ከእግዚአብሔርም ከሰውም በረከት ያገኛሉ እናንተ ደግሞ በአባ ገብረ ናዝራዊ ዘመን 1ሺህ 5መቶ የሚሆኑ መነኮሳት በአጋንቺ ኪዳነ ምህረት የሚጸልዩበት የቅዱሳን ልጆችና የበረከት ፍሬዎች ናችሁ ብለዋል።

አምላካችን እግዚአብሔር ሰው በጠፋበት ጊዜ እንደ ሙሴ አይነት መልካሞችን በማስነሳት እስራኤላውያንን ነጻ እንዳወጣቸው ሁሉ ይኽንን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በመገንባት ለፍጻሜ ያበቃችሁ የሕንጻ አሰሪ ኮሚቴዎች ፣ የከተማዋ ነዋሪዎችና በተለያዩ ቦታዎች ለሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች የዘመናችን ሙሴዎች ናችሁ ሲሉ ብፁዕነታቸው ምስጋና አቅርበዋል።

በተመሳሳይ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በሰጡት ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ ብዙዎች እናንተን ለማየት ሽተው አላዩም እናንተንና በሁሉ ነገር የደከማችሁበትን የድካማችሁ ፍሬ የሆነውን ይኽን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን የሰሙ ጆሮዎቻችን ፣ ያዩ አይኖቻችንና የረገጡ እግሮቻችን የተባረኩ ናቸው በዓሉን ከናንተ ጋር በማክበራችን በእጅጉ ተደስተናል እናንተም እንኳን ለዚህ አበቃችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

መንዝና አካባቢው የነገስታት መሰወሪያና በዮዲት ጉዲት ዘመን ያልታቀጠሉ አብያተ ክርስቲያናት መገኛ ነው ያሉት ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ

በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ እንዳለ ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት እናንተም በእምነት ፣ በእውቀትና በእውነት የተወለዳችሁ  የቅዱሳን ልጆች ናችሁ ብለዋል። 

"ያገለግለኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ" በሚል ርዕስ የዕለቱን ወንጌል ያስተማሩት የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ክቡር መጋቤ ሐዲስ ነቅዐጥበብ አባቡ በችግር ምክንያት ወደ ግብጽ የተሰደዱት እስራኤላውያን ለ430 ዓመታት በስቃይና በመከራ ቆይተው አምላካችን እግዚአብሔር በሙሴ አማካኝነት ሌሊቱን በብርሃነ እሳት ቀኑን በደመና በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት ከፈርኦን ግዛት ነጻ መውጣታቸውን ገልጸው ዛሬም እንደፈርኦን በሀገራችን ደም የጠማቸውን ደም አፍሳሾች አምላከ ቅዱሳን ያስታግስልን ሲሉ በስፋትና በምልአት አስተምረዋል።

የሕንጻ አሰሪ ኮሚቴ ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ካሳዬ ወልደ ማርያም ባቀረቡት ሪፖርት የዛሬው ቀን ዓመታትን ያስቆጠረው ጭንቀታችን እልባት ያገኘበትና በመተባበር ተአምር መስራት እንደምንችል ከብዙ ድካም በኋላ ያስመሰከርንበት የድል ቀን ሲሆን የዚህ ካቴዲራል የማስፋፋትና የእድሳት ስራ ሊጠናቀቅ የቻለው በጸሎትና በእቅድ መመራቱ መሆኑን ጠቁመውና እስካሁን ግንባታው ፰ ነጥብ ፪ ሚሊዮን ብር መፍጀቱን ገልጸው ለግንባታው የገንዘብ ፣ የአይነት ፣ የገንዘብና የጉልበት ድጋፍ በውጭና በሀገር ውስጥ ለሚገኙ የአካባቢው ተወላጆችና ለመሀል ሜዳ ከተማ ነዋሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።

ለግንባታው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላ የሽልማትና የሰርተፍኬት ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።

የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በታሪክ የታወቁ በዓለም የተደነቁ አድባራትና ገዳማት መገኛ ሲሆን ከነዚህም መካከል የመሀል ሜዳ ደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴዲራል አንዱ ነው።






No comments: