Sunday, May 31, 2020

በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በዕቅድ ያለመመራትን ችግር ሊቀረፍ የሚችል የዳሰሳ ጥናት ሊካሄድ ነው።


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስበከት በየደረጃው የሚታየውን በዕቅድ ያለመመራት ችግር በዘላቂነት ሊፈታ የሚችል የዳሰሳ ጥናት የሚያካሂድ ኮሚቴ በብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ አባታዊ መመሪያ ተቋቁሞ ሥራ ጀምሯል።

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያና የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለአጥኒ ኮሜቴው በሰጡት የሥራ መመሪያ ተግባሩን ቀድመን ለመጀመር ፍላጎት ፣ ፈቃደኛነቱና አቅሙ ቢኖረንም በተለያዩ ፈተናዎች መዘግየቱን አውስተው አሁንም ስላልመሸ ኮሚቴው በፍጥነት ወደ ተግባር መግባት አለበት ብለዋል።
  
አባቶቻችን መስዋዕትነት በመክፈል ያስረከቡንን ቤተ ክርስቲያንና ሀገር እኛም ለተተኪው ትውልድ አዳጊ በሆነ መንገድ ማስረከብ አለብን ያሉት ብፁዕነታቸው ሥራው ሲጀመር አልጋ በአልጋ ሊሆን ስለማይችል እና ያለፈተናና ያለድካም የሚገኝ ፍሬና ውጤት ስለሌለ አስፈላጊውን ዋጋ በመክፈል ጥናቱን ለውጤት ማብቃት አለባችሁ ሲሉ ለኮሚቴው አባታዊ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ቤተ ክርስቲያን የውስጥና የውጭ ፈተና እንዳለባት አውስተው መጀመሪያ የውስጡን ፈተና አርመን ውስጡን ንጹሕ በማድረግ የውጩን ፈተና በጋራና በጥበብ እንከላከለዋለን ብለዋል።

ለዕቅድ ዝግጅት ሥራው የዳሰሳ ጥናት የሚያካሂደው ኮሚቴ የተቋቋመው በብፁዕነታቸው አባታዊ መመሪያ መሆኑን የገለጹት የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ ነቅዐጥበብ አባቡ በሀገረ ስበከቱ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው በዚህ ዓመት ብቻ 45 የአብነት መምህራን እንደተቀጠሩና የዳሰሳ ጥናቱ መካሄድ የቤተ ክርስቲያንንና የአገልጋዮቿን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍና ለ5 ዓመቱ ስትራቴጂክ ዕቅድ እንደግብዓት ለመጠቀም ፋይዳው የጎላ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ልማትና ዕቅድ መምሪያ ኃላፊ ሊቀ ካህናት ሀብተ ጊዮርጊስ ዘውዱ በቤተ ክርስቲያናችን የሚታየውን በዕቅድ ያለመመራት ችግር በመቅረፍ በብፁዕነታቸው መመሪያ መሰረት ሀገረ ስብከታችን በዕቅድ በመምራት ለሌሎች ሀገረ ስብከቶች አርዓያ ለመሆን በሚያስችል መልኩ ዐቢይ ኮሚቴና የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ ቅጻቅጾችን በማዘጋጀት ሲሰራ እንደቆየ ገልጸዋል።
የዳሰሳ ጥናቱ በ10 ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ያተኮረ ሲሆን በ18 ወረዳ ፣ በ7 ገዳማትና በ5 የአብነት ትምህርት ቤቶች ከግንቦት 25 ጀምሮ እንደሚካሄድና በዚህ መነሻ ጥናትም የ5 ዓመት እስትራቴጂክ ዕቅድ በሰኔ ወር ይታቀዳል ሲሉ ተናግረዋል።
የዳሰሳ ጥናቱን የሚያካሂዱት የኮሚቴ አባላት ከብፁዕነታቸው የተሰጣቸውን አባታዊ የሥራ መመሪያ በመቀበል ለተግባራዊነቱ የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።


No comments: